ገጣሚ: ገመቹ በቀለ ለሙ
ሄ ሄ ዬ ኢም… የሀገር ፍቅር አልከኝ ልጄ… (አሄ የራብ)
ፍቅር ምንድነው ትርጉሙ
ነጻነትስ አለው ወይ ፍቺ
በተግባር ወሎ ካልታየ
የቃላት ጋጋታ ነው ‘ንጂ።
ፍቅርስ ፍቅር ከሆነ
ነጌ የሚመጣውን አይፈራም
አንደዛ…. ሞኝ ተላላ
ቤት አሸዋ ላይ አይሰራም
ነጻነት ነጻ ከሆነ አውነትም ነጻነት ካለው
ራስ ወዳጅ መሆን አይችልም ለሁሉም ነጻነት አለው።
ይህች ሀገር ኢትዮጵያ፤ አምላክም ያለቅስላታል… እንዲህ እያለ
“ለአንድነት ልስራ የሚለው፣ ውድቀትን ያበጅላታል፣
የነጻነት አንደራሴው ራሱ ነጻነት ጎሎታል!”
ይህችን ሀገር ይችን ምስኪን አምላክም ያለቀሰላታል
ማ………………………………….ናችው
ልጆች፤ ደበበ፣ ጫላ፣ ክብሮም
መሐመድ፣ ቆጭቶ፣ ኡጁሉ፣ ዬት ናችሁ?
አንድ ነገር ልንገራችሁ…
(ጉርባ ዋ አት ናቅጭ፣ ዋ አት ናቅጭ)
አንድነትን ማን ይጠላል፣ አንድነት ጥሩ ነገር ነው
ግን፣ በአንድነት በግ ቆዳ ውስጥ ያለው ሌላ ተኩላ ነው
ኢትዮጵያ አንድ ትሆን ብዬ
ግጥም ገጥሜ ቢጨፍር
አንድነት ፍቅር ነው ብዬ
ባማረ ዜማ ቢዘምር….ምን ዋጋ አለው፣ ምን ምን ዋጋ አለው!!
ወንድሜ ጫላ ሲናገር አንተ ዘረኛ ብለው
የብሄርተኝነት ቁምጣ፣ እጀ-ጠባብ ባለብሰው
አበቤን ነፍጠኛ ብዬ እራሴ ነፍጥ ባነሳ
የራሴን ጥፋት ደብቄ ዝንት የሱን ክፋት ባወሳ
ሁሴንን በእምነቱ ሰበብ
ኡጁሉን በደም ባጥንቱ፣በቅላጼ አነጋገሩ
የምስቅበት ከሆነ፤
አንድነት ጋጋታ ይሆናል፣ ፍቅርም ባዶ ነው ቅሉ።
ተራራ፣ ወንዝና ዱሩ
ሀገር መውደድ ትርጉም ያለው፣
ተራራው ላይ የሚያርስ ሰው
ከወንዙ ዓሣ የሚያጠምደው
ከዱሩ ማር የሚቆርጠው
እርሱ ክብር ሲኖረው ነው።
በርግጥ ህግ የበላይ ነው
ግን….
ህግ የሰው አገልጋይ ነው
ሰውን የሚያገለግል ህግ
አገልጋይ መሆን ከረሳ
ሰው ህግ ማክበሩ ለምኑ
ከጠፋ መብትና ክብሩ!?
ነጻነት ውሃ ከሆነ፣ ታሪክን መልሶ መቅዳት
የደፈረሰውን ኩሬ ወንዝ፣ ንጹህ ነው ብሎ ማጠጣት
እሱ ነጻነት አይደለም፣ በነጻነት ሥም ንግድ ነው
የመተሳሰብ ማጠፊያ፣ ራስን የመውደድ ግምብ ነው።
ነጻነት ይቅር ካላለ
የታሪክ ጥፋት አሻራን፣
ፊታችን ማልበሱ አይቀርም
ሌላ የጥፋት አዋራ
ይህች ሀገር፣ ይህች ኢትዮጵያ
ኤሬ ምን ይሻላታል?
የልጆችዋን ውሎ እያየ
አምላክም ያለቅስላታል!
(ዬ ራቢ ሜ ኢት ቅጭ ኣቤ ሜ ኢት ቅጭ)